እስልምና ከሳይንስ ጋር ይቃረናልን?

የእስልምና መጽሐፍ የሆነው ቁርዓን ከፈጣሪ ዘንድ ለሰው ልጆች በማሳረጊያነት የወረደላቸው መጽሐፍ ሲሆን ለነቢያት በሚወፈቁ የመገለጥ መሰጠቶችም የመጨረሻው ዝርያ ነው።

ምንም እንኳን (ከ1400 ዓመታት በፊት የወረደው) ቁርዓን በዋነኛነት የሳይንስ መጽሐፍ ባይሆንም፥ በቴክኖሎጂ እና በሳይንሳዊ ዕውቀት መመንደግ የተነሳ በቅርብ ጊዜ ብቻ ሊረጋገጡ የቻሉ ሳይንሳዊ እውነታዎችን ይዟል። እስልምና ማሰላሰልን እና ሳይንሳዊ ምርምርን ያበረታታል። ምክንያቱም የስነ ፍጥረትን ምንነት መገንዘብ ሰዎች ፈጣሪያቸውንና የፈጣሪያቸውን የኃይል እና የጥበብ መጠን ይበልጥ እንዲያደንቁ ያስችላቸዋል።

ቁርዓን የወረደው ሳይንስ ገና በሚድህበት ጊዜ ነበር፤ ቴሌስኮፖች፣ ማይክሮስኮፖች አልያም ከዛሬ ዘመን ቴክኖሎጂ ጋር የሚቀራረብ አንዳችም ነገር አልነበረም። ፀሐይ በመሬት ዙሪያ እንደምትዞር እና ዝርግ በሆነች ምድር ማዕዘናት ላይ የሚገኙ ዓምዶች ሰማይን ደግፈው እንዳቆሙት ሰዎች ያምኑ ነበር። እንግዲህ ይህ በነበረበት ሁኔታ ነው ቁርዓን ከሥነ ፈለክ እስከ ሥነ ሕይወት፣ ከከርሰ ምድር ጥናት እስከ ሥነ እንስሳት ድረስ ባሉ ርዕሰ ጉዳዮች ዙሪያ በርካታ ሳይንሳዊ እውነታዎችን ይዞ የወረደው።

በቁርዓን ውስጥ ከሚገኙ በርካታ ሳይንሳዊ እውነታዎች መካከል የሚከተሉት ይገኙበታል፤

እውነታ #1 - የሕይወት ስርዎ ምንጭ

እነዚያም የካዱት ሰማያትና ምድር የተጣበቁ የነበሩና የለያየናቸው መሆናችንን አያውቁምን? ሕያው የሆነንም ነገር ሁሉ ከውሃ ፈጠርን። አያምኑምን?

ቁራኣን - 21:30
(ፍቹ ሲተረጎም)

የህይወት ሁሉ መነሻ ውሃ መሆኑ ተጠቁሟል። ሕይወት ያላቸው ነገሮች በሙሉ የተሠሩት ከህዋሶች ሲሆን ህዋሶች ደግሞ አብዛኛው ስሪታቸው ከውኃ እንደሆነ በአሁን ጊዜ እናውቃለን። ይህ ግን ሊረጋገጥ የቻለው ማይክሮስኮፕ ከተፈለሰፈ በኋላ ብቻ ነበር። በአረብ በረሃማ ምድር፥ ሕይወት ሁሉ ከውኃ መገኘቱን የሚገምት ሰው ይኖር ነበር ብሎ ማሰብ የማይመስል ነገር ነው የሚሆነው።

እውነታ #2 - የሰው ልጅ ፅንስ እድገት

ስለ ሰው ልጅ የፅንስ እድገት ደረጃዎች አሏህ ይናገራል፤

በእርግጥም ሰውን ከነጠረ ጭቃ ፈጠርነው። ከዚያም በተጠበቀ መርጊያ ውስጥ የፍትወት ጠብታ አደረግነው። ከዚያም ጠብታዋን (በአርባ ቀን) የረጋ ደም አድርገን ፈጠርን። የረጋውንም ደም ቁራጭ ሥጋ አድርገን ፈጠርን። ቁራጯንም ሥጋ አጥንቶች አድርገን ፈጠርን። አጥንቶቹንም ሥጋን አለበስናቸው። ከዚያም (ነፍስን በመዝራት) ሌላ ፍጥረትን አድርገን አስገኘነው። ከሰዓሊዎችም ሁሉ በላጭ የሆነው አላህ ላቀ።

ቁራኣን - 23:12-14
(ፍቹ ሲተረጎም)

"አላቃህ" የሚለው የአረብኛ ቃል ሶስት ፍችዎች አሉት፥ አልቀት፣ የተንጠለጠለ ነገር እና የደም መርጋት። "ሙድጋህ" ማለት የታኘከ ነገር ማለት ነው። የኢምብሪዮሎጂ ሳይንቲስቶች የፅንስ አፈጣጠርን በመግለፅ ረገድ የእነዚህ ቃላት አጠቃቀም ትክክለኛ እና አሁን ላይ ካለን የፅንስ አስተዳደግ ሂደት ሳይንሳዊ ግንዛቤ ጋር የሚጣጣም መሆኑን አስተውለዋል።

ስለ ሰው ልጅ ፅንሶች ደረጃ በደረጃ እድገት እና አከፋፈል እስከ ሃያኛው መቶ ክፍለ ዘመን ድረስ የሚታወቀው ጥቂት ነገር ብቻ ነበር። ይህም ማለት፥ ቁርዓን ስለ ሰው ልጅ ፅንስ ያቀረባቸው ዝርዝር ገለፃዎች በሰባተኛው መቶ ክፍለ ዘመን በነበረ ሳይንሳዊ እውቀት ላይ የተመሰረቱ ሊሆኑ አይችሉም።

እውነታ #3 - የአጽናፈ ዓለሙ መለጠጥ

የሥነ ፈለክ ሳይንስ ገና ይድኽ በነበረበት ዘመን፥ የሚከተለው የቁርዓን አንቀጽ ተገልፆ ነበር፤

ሰማይንም በኃይል ገነባናት። እኛም በእርግጥ ቻዮች ነን።

ቁራኣን - 51:47
(ፍቹ ሲተረጎም)

ከላይ የቀረበው አንቀፅ ካሉት ታላሚ ፍችዎች መካከል አንዱ አሏህ አፅናፈ ዓለሙን (ማለትም፥ ሰማየ ሰማያትን) እያስፋፋው መሆኑ ነው። ሌሎች ፍችዎች ደግሞ አሏህ ለአጽናፈ ዓለሙ የሚያስፈልገውን ነገር የሚያሟላለትና በእሱም ላይ ኃያልና ቻይ የመሆኑ ጉዳይ ነው። እነዚህም እውነት ናቸው።

አጽናፈ ዓለሙ እየተለጠጠ የመሆኑ (ለምሳሌ፥ ፕላኔቶች እርስበርሳቸው ይበልጥ እየተራራቁ በመሄድ ላይ ናቸው) እውነታ የተደረሰበት በባለፈው ምዕተ ዓመት ነበር። የፊዚክስ ሊቁ ስቴፈን ሆኪንግ 'ኤ ብሪፍ ሂስትሪ ኦቭ ታይም' በሚለው መጽሐፉ "አጽናፈ ዓለሙ በመለጠጥ ላይ የመሆኑ ግኝት ከሃያኛው መቶ ክፍለ ዘመን ታላላቅ የእውቀት አብዮቶች መካከል አንዱ ነው" ሲል ጽፏል።

ቁርዓን ቴሌስኮፕ ከመፈልሰፉ ጭምር ነው ስለ አፅናፈ አለሙ መስፋፋት የሚያወሳው!

እውነታ #4 - የብረት ከሰማይ መውረድ

ብረት ለመሬት ባዕድ የሆነ ማዕድን ሲሆን ወደዚህች ፕላኔት የመጣው ከውጨኛው የሕዋ ክፍል ነው። ፈነድተው ከተበታተኑ ሩቅ ከዋክብት የሰበሰቡትን ብረት በተሸከሙ ሚትሪዮራይቶች በቢሊዮን ከሚቆጠሩ ዓመታት በፊት መሬት ተመትታ እንደነበር ሳይንቲስቶች ደርሰውበታል።

. . . ብረትንም በውስጡ ብርቱ ኀይልና ለሰዎችም መጠቃቀሚያዎች ያልሉበት ሲሆን አወረድን። . . .

ቁራኣን - 57:25
(ፍቹ ሲተረጎም)

አሏህ 'አወረድን' የሚልን አገላለፅ ይጠቀማል። ብረት ከውጨኛው የሕዋ ክፍል ወደ ምድር የወረደ ማዕድን የመሆኑ እውነታ በሰባተኛው መቶ ክፍለ ዘመን በነበረው ኋላቀር ሳይንስ ሊታወቅ የሚችል አልነበረም።

እውነታ #5 - የሰማይ ከለላነት

ምድሪቱን እና ነዋሪዎቿን ከአጥፊ የፀሐይ ጨረሮች ብሎም ከአስከፊ የሕዋ ቅዝቃዜ በመጠበቅ ረገድ ሰማይ ወሳኝ ሚና ይጫወታል።

አሏህ በሚከተለው የቀርዓን አንቀፅ ሰማይን እንድናጤን ይጠይቀናል፥

ሰማይንም (ከመውደቅ) የተጠበቀ ጣራ አደረግን። እነርሱም ከተዓምራቶቿ ዘንጊዎች ናቸው።

ቁራኣን - 21:32
(ፍቹ ሲተረጎም)

የሰማይ ከለላነት እንደ አንድ የአሏህ ምልክት ተደርጎ በቁርዓን ተጠቁሟል። በሃያኛው ክፍለ ዘመን በተደረጉ ሳይንሳዊ ምርምሮች ነው ሰማይ የከለላነት ባህሪያት እንዳሉት የተገኘው።

እውነታ #6 - ተራሮች

አሏህ አንድን ወሳኝ የሆነ የተራሮች ጠባይ ልብ እንድንል ያመላክተናል፤

ምድርን ምንጣፍ አላደረግንምን? ጋራዎችንም ችካሎች አላደረግንምን?

ቁራኣን - 78:6-7
(ፍቹ ሲተረጎም)

ቁርዓን "ችካሎች" የሚለውን ቃል በመጠቀም ነው የተራሮችን ጥልቅ ሥሮች በትክክል የሚገልፀው። ለምሳሌ ያህል የኤቨረስት ተራራ ከመሬት በላይ ወደ 9 ኪሎ ሜትር የሚጠጋ ከፍታ ሲኖረው፥ ሥሩ ግን ከ125 ኪሎ ሜትር በላይ ጥልቀት አለው!

ተራሮች ጥልቅ 'ችካል' መሰል ስሮች ያሏቸው መሆኑ የፕሌት ቴክቶኒክስ ንድፈ-ሀሳብ ካደገበት የሃያኛው ክፍለ ዘመን መባቻ በኋላ እንጂ ከዚያ በፊት አይታወቅም ነበር። አሏህም በቁርዓን ውስጥ "... በእናንተ እንዳታረገርግ" (16፡15) ብሎ እንደገለፀው ተራሮች ምድርን እንዳትዋልል የማረጋጋት ሚና አላቸው። ሳይንቲስቶች ይህን ገና መረዳት መጀመራቸው ነው።

እውነታ #7 - የፀሐይ ምህዋር

በ1512 የሥነ ፈለክ ተመራማሪው ኒኮላስ ኮፐርኒከስ ፀሐይ በሶላር ሲስተሙ እምብርት ላይ ረግታ መቆሟን እና ፕላኔቶችም በዙሪያዋ እንደሚሽከረከሩ የሚያስረዳ ፅንሰ-ሀሳቡን አቀረበ። ይህ አስተሳሰብ በሥነ ፈለክ ተመራማሪዎች ዘንድ እስከ ሃያኛው ክፍለ ዘመን ድረስ የተንሰራፋ ነበር። ነገር ግን ፀሐይ የቆመች ሳትሆን በሚልኪ ዌይ ጋላክሲያችን እምብርት ዙሪያ የተዘረጋን ምህዋር ተከትላ የምትሽከረከር መሆኗ አሁን ላይ በሚገባ የተረጋገጠ ሃቅ ነው።

እርሱም ሌሊትንና ቀንን፣ ፀሐይንና ጨረቃንም የፈጠረ ነው። ሁሉም በፈለካቸው ውስጥ ይዋኛሉ።

ቁራኣን - 21:33
(ፍቹ ሲተረጎም)

እውነታ #8 - የውቅያኖስ ውስጣዊ ሞገዶች

ሞገዶች በውቅያኖስ የላይኛው ገፅ ላይ ብቻ እንደሚከሰቱ ነበር በተለምዶ የሚታሰበው። ይሁን እንጂ በውስጠኛው ክፍል የሚከሰቱ በሰው ልጅ ዓይን የማይታዩና በተራቀቁ ልዩ መሣሪያዎች ብቻ መታወቅ የሚችሉ ውስጣዊ ሞገዶች መኖራቸውን የውቅያኖስ ተመራማሪዎች ደርሰውበታል።

ቁርዓን እንዲህ ይላል፡-

ወይም (መጥፎ ሥራዎቻቸውን) ከበላዩ ደመና ያለበት ማዕበል በሚሸፈነው ጥልቅ ባህር ውስጥ እንዳሉ ጨለማዎች ነው። (እነዚያ) ከፊላቸው ከከፊሉ በላይ ድርብርብ የሆኑ ጨለማዎች ናቸው። . . .

ቁራኣን - 24:40
(ፍቹ ሲተረጎም)

ይህ ገለፃ የሚያስደንቅ ነው። ምክንያቱም ከ1400 ዓመታት በፊት በጥልቅ ውቅያኖሶች ሆድ የሚገኙ ውስጣዊ ሞገዶችን ለማወቅ የሚያስችል ልዩ መሳሪያ አልነበረም።

እውነታ #9 - ውሸት እና እንቅስቃሴ

በነብዩ ሙሐመድ (ሰላም በእርሳቸው ላይ ይሁን) ዘመን የኖረ አንድ ጨካኝና ጨቋኝ የጎሳ መሪ ነበር። አሏህም እሱን የሚገስፅ አንድ የቁርዓን አንቀጽ አወረደ፤

ይተው ባይከለከል አናቱን ይዘን እንጎትተዋለን። ውሸታም ስሕተተኛ የሆነችውን አናቱን።

ቁራኣን - 96:15-16
(ፍቹ ሲተረጎም)

አሏህ ይህንን ሰው ውሸታም አይለውም። ግንባሩን (የአንጎሉን የፊተኛ ክፍል) ነው 'ውሸታም' እና 'ኃጢአተኛ' በማለት ያንን ማድረግ እንዲያቆም የሚያስጠነቅቀው። በርካታ ጥናቶች እንዳረጋገጡት የአንጎላችን የፊተኛው ክፍል (ፍሮንታል ሎብ) ነው ለውሸትም ሆነ በፈቃደኝነት ላይ ለተመሰረተ እንቅስቃሴ (በዚያውም ለኃጢአት) ተጠያቂው። እነዚህ የአንጎል ተግባሮች ሊታወቁ የቻሉት በሃያኛው መቶ ዘመን በተፈበረከ ምስላዊ የሕክምና መሣሪያ እገዛ ነው።

እውነታ #10 - የማይቀላቀሉት ሁለቱ ባህሮች

ባሕሮችን በተመለከተ ፈጣሪያችን እንዲህ ይላል፤

ሁለቱን ባሕሮች የሚገናኙ ሲሆኑ ለቀቃቸው፤ (እንዳይዋሐዱ) በመካከላቸው ጋራጅ አልለ። (አንዱ ባንዱ ላይ) ወሰን አያልፉም።

ቁራኣን - 55:19-20
(ፍቹ ሲተረጎም)

ሰርፌስ ቴንሽን የሚባል አካላዊ ኃይል ተጎራባች ባሕሮችን ውሃቸው እንዳይቀላቀል ያግዳቸዋል - በውሃዎቹ መካከል በሚኖር የእፍግታ ልዩነት የተነሳ። ልክ በመካከላቸው ስስ ግድግዳ ያለ ይመስል። ይህ እውነታ በውቅያኖስ ተመራማሪዎች የተደረሰበት በጣም በቅርብ ጊዜ ነው።

ቁርዓን የነብዩ መሐመድ የፈጠራ ድርሰት ሊሆን አይችልም ነበርን?

ነቢዩ ሙሐመድ (ሰላም በእርሳቸው ላይ ይሁን) መሐይም የነበሩ ስለመሆናቸው በታሪክ የሚታወቅ ሐቅ ነው። እርሳቸው ማንበብም ሆነ መፃፍ የማይችሉ ነበሩ። እንዲሁም በቁርዓን ውስጥ ከሚገኙ ሳይንሳዊ ትክክለኛነታቸው የሰመረ ጉዳዮች ጋር ግንኙነት ሊኖረው በሚችል አንድም የሙያ መስክ ስልጠና አልወሰዱም።

ምናልባትም አንዳንዶች በዘመናቸው ከነበሩ ቀለም አዋቂዎች ወይም ሳይንቲስቶች የቀዱት ነው ይሉ ይሆናል። ከሌላ ምንጭ ተቀድቶ ቢሆን ኖሮ የወቅቱን የተሳሳቱ ሳይንሳዊ ግምቶች በሙሉ አብረው ተገልብጠው ለማግኘት እንጠብቅ ነበር። ይልቁንስ ቁርዓንን በውስጡ ምንም አይነት ስህተት - ሳይንሳዊም ሆነ ሌላ አይነት - የሌለበት ሆኖ ነው የምናገኘው።

ሌሎች ሰዎች ደግሞ ምናልባትም አዳዲስ ሳይንሳዊ እውነታዎች በታወቁ ቁጥር ቁርዓን ለውጥ ተደርጎበታል ይሉ ይሆናል። ይህ ግን ሊሆን አይችልም፤ ምክንያቱም ቁርዓን መጀመሪያ በወረደበት ቋንቋ ተጠብቆ መቆየቱ በታሪክ ተሰንዶ የሚገኝ እውነታ ነው። ይህም በራሱ አንድ ተዓምር ነው።

ይህ እንዲሁ ያልታሰበ መገጣጠም ቢሆንስ?

እርሱም (ቁርኣን) እውነት መሆኑ ለእነርሱ እስከሚገለፅላቸው ድረስ በአጽናፎቹ ውስጥና በነፍሶቻቸውም ውስጥ ያሉትን ተዓምራቶቻችንን በእርግጥ እናሳያቸዋለን። ጌታህም እርሱ በነገሩ ሁሉ ላይ ዐዋቂ መሆኑ አይበቃቸውምን?

ቁራኣን - 41:53
(ፍቹ ሲተረጎም)

ምንም እንኳ ይህ ምላሽ ሳይንሳዊ ተዓምራት ላይ ብቻ ያተኮረ ቢሆንም፥ በርካታ ተጨማሪ የተዓምራት ዓይነቶች - ታሪካዊ ተዓምራት፣ የተፈፀሙ ትንቢቶች፣ አቻ የማይገኝላቸው ስነ ልሳናዊና ሥነ ጽሑፋዊ ስልቶች፣ ወዘተ. - በቁርዓን ውስጥ ተወስተው ይገኛሉ። ይህ እንግዲህ በሚያነቡት ሰዎች ላይ ቁርዓኑ የሚያሳድረውን ልብን በከፍተኛ ደረጃ የመንካት ኃይል ሳይጨምር ነው። እነዚህ ሁሉ ተዓምራት ያልታሰበ መገጣጠም ያስከተላቸው ክስተቶች ሊሆኑ አይችሉም። ይልቁንስ ቁርዓን የእነዚህ ሁሉ የሳይንስ ህግጋት ፈጣሪ ከሆነው ከአሏህ የወረደ መሆኑን በግልጽ ያመለክታሉ። እሱ ሁሉንም ነቢያት ተመሳሳይ መልዕክትን - አንዱን አሏህ ብቻ መገዛትና የመልክተኛውንም አስተምህሮዎች መከተል - አስይዞ የላካቸው ያው አንድዬ አምላክ ነው።

ቁርዓን አሏህ የሰው ልጆችን በዓላማ ቢስነት ዝም ብለው እንዲንከላወሱ እንዳልፈጠራቸው የሚያስረዳ ተግባራዊ መምሪያ መጽሐፍ ነው። ይልቁንስ ህይዎታችን ትርጉም አዘልና የላቀ አላማ እንዳለው - የአሏህን እንከን የለሽ ፍፁምነት፣ ታላቅነት እና ብቸኝነት እንድናውቅና ለእርሱም እንድንታዘዝ - ያስተምረናል።

ከምልክቶች ሁሉ እጅግ በጣም ወሳኙ ምልክት ቁርዓን ሆኖ ሳለ፥ እያንዳንዱ ሰው የአሏህን ምልክቶች ለማሰላሰልና ለመገንዘብ በአሏህ የሚመራ አዕምሮውን እና የማመዛዘን ችሎታውን ይጠቀም ዘንድ ሃላፊነት አለበት። የቁርዓንን ውበትና እውነተኛነት አንብባችሁ ድረሱበት - ስኬትን ትጎናፀፉ ዘንድ።

ምንጭ: islamicpamphlets.com
ትርጉም በ: Abdu Ahmed