እስልምና ስለ ሽብርተኝነት ምን ይላል?

የምህረት ሐይማኖት የሆነው እስልምና ሽብርተኝነትን አይፈቅድም። በቁርዓን ውስጥ አሏህ ይህን ብሏል፤

ከእነዚያ በሃይማኖት ካልተጋደሏችሁ ከአገሮቻችሁም ካላወጡዋችሁ (ከሓዲዎች) መልካም ብትውሉላቸውና ወደእነርሱ ብታስተካክሉ አላህ አይከለክላችሁም፡፡ አላህ ትክክለኞችን ይወዳልና፡፡

ቁራኣን - 60:8
(ፍቹ ሲተረጎም)

ነብዩ ሙሐመድ (ሰላም በእርሳቸው ላይ ይሁን) ሴቶችን እና ልጆችን ከመግደል እንዲታቀቡ ወታደሮችን ይከለክሏቸውና እንዲህ ሲሉም ይመክሯቸው ነበር፤

ከዳተኛ አትሁኑ፤ ቆዳንም አትተልትሉ፤ ልጅንም አትግደሉ።

Jami` at-Tirmidhi, 1408

በተጨማሪም ይህን ብለዋል፤

ከሙስሊሞች ጋር የሰላም ውል ያለውን ሰው የገደለ የጀነትን ሽታ አያሸታትም - ምንም እንኳ ሽታዋ ከአርባ ዓመታት ርቀት ላይ የሚታወቅ ቢሆንም።

Sahih al-Bukhari, 3166

እንዲሁም ነቢዩ ሙሐመድ (ሰላም በእርሳቸው ላይ ይሁን) በእሳት መቅጣትን ከልክለዋል።

በአንድ ወቅት ግድያን ከታላላቅ ኃጢዓቶች ዝርዝር ውስጥ በሁለተኛነት ጠቅሰውት ያውቃሉ፤ አልፎም ተርፎም ስለመጨረሻው የፍርድ ቀን እንዲህ ሲሉ አስጠንቅቀዋል፤

(በትንሣኤ ቀን) በቅድሚያ የፍርድ ውሳኔ የሚያገኙት ጉዳዮች የደም መፋሰስ ጉዳዮች ናቸው።

Sahih al-Bukhari, 6533

እንዲያውም ሙስሊሞች ለእንስሳት እንዲራሩ ይበረታታሉ፤ እንዳያሰቃዩዋቸውም ተከልክለዋል። በአንድ ወቅት ነብዩ ሙሐመድ (ሰላም በእርሳቸው ላይ ይሁን) እንዲህ ብለዋል፥

አንዲት ሴት አስራ ባቆየችው ድመት ምክንያት ለ(ጀሐነም) እሳት ተዳርጋለች፤ ወይ ምግቡን አልሰጠችው አልያም የምድር ነፍሳትን ፈልጎ እንዳይበላ ነፃ አላደረገችው።

Sahih al-Bukhari, 3318

አንድ ሰው በጣም ለተጠማ አንድ ውሻ የሚጠጣው ውሃ ሰጥቶ በዚህ ተግባሩ ምክንያት አሏህ ወንጀሎቹን ማረውም ብለዋል። ነብዩ (ሰላም በእርሳቸው ላይ ይሁን) “የአሏህ መልእክተኛ ሆይ፥ ለእንስሳት ርህራሄን በማሳየታችን ምንዳ እናገኛለን?” ተብለው ተጠይቀው ነበር። እርሳቸውም እንዲህ አሉ፥

ሕይወት ላለው ለእያንዳንዱ እንስሳም ሆነ የሰው ልጅ ለሚፈፀም የደግነት ተግባር ምንዳ አለ።

Sahih al-Bukhari, 2466

በተጨማሪም፥ ሙስሊሞች እንስሳን ለምግብነት በሚያርዱበት ወቅት በተቻለ መጠን እንስሳውን በማያስፈራራና ብዙም በማያሰቃይ መንገድ እንዲሆን ታዝዘዋል። ነቢዩ ሙሐመድ (ሰላም በእርሳቸው ላይ ይሁን) እንዲህ ብለዋል፥

እርድ በምትፈፅሙ ጊዜ በአግባቡ ፈፅሙት። ከእናንተ መሐል እርድ ሊፈፅም የተነሳ ሰው ካራውን በደንብ ይሳል፤ ለእንስሳውም (ከእርዱ በፊት) ምቾትን ይለግሰው።

Jami` at-Tirmidhi, 1409

ከነዚህና ከሌሎች የእስልምና መዛግብት አንፃር፥ ምንም የማያውቁ ሰላማዊ ሰዎች ልብ ውስጥ ሽብርን የመንዛት ተግባር፣ ተቋማትንና ንብረትን በጅምላ ማውደም፣ በንጹሃን ወንዶች፣ ሴቶችና ህጻናት ላይ የቦምብ ጥቃትና የአካል ጉዳት ማድረስ ሁሉም ክልክል ከመሆናቸው ባሻገር በእስልምናም ሆነ በሙስሊሞች ዘንድ የሚጠሉ ፀያፍ ድርጊቶች ናቸው።

ሙስሊሞች የሰላም፣ የእዝነት እና የይቅር ባይነት ሐይማኖትን ነው የሚከተሉት። እጅግ አብዛኛው ምዕመንም አንዳንዶች ከሙስሊሞች ጋር በሚያገናኟቸው ደም አፋሳሽ ሁነቶች ውስጥ እጁ የለበትም። አንድ ሙስሊም ግለሰብ የሽብር ተግባር ልፈጽም ቢል፥ ይህ ሰው የእስልምናን ህግጋት በመጣስ ሐጢዓተኛ ይሆናል።

ይሁን እንጂ፥ ሽብርተኝነትን ወረራን ለመቋቋም ከሚደረግ ህጋዊ ተጋድሎ ነጥሎ መመልከት አስፈላጊ ነው - እነዚህ ሁለቱ የተለያዩ ጉዳዮች ስለሆኑ።

ምንጭ: islam-guide.com · islamicpamphlets.com
ትርጉም በ: Abdu Ahmed

ተመሳሳይ ጥያቄዎች