ሙስሊሞች ምን ምን በዓላትን ያከብራሉ?

ሙስሊሞች ሁለት ዒዶችን (በዓላትን) ብቻ ያከብራሉ፤ በረመዷን ወር ማጠናቀቂያ የሚከበረው ዒድ አል-ፊጥርን እና የሐጅ ስነስርዓት (ዓመታዊ የመንፈሳዊ ጉዞ ወቅት) መጠናቀቁን በሚያበስረው በዙል-ሂጃህ ወር 10ኛ ቀን የሚከበረው ዒድ አል-አድሃን።

በእነዚህ ሁለት በዓላት ሙስሊሞች እንኳን አደረሰህ/ሽ ይባባላሉ፤ በየቀያቸው የደስታ መግለጫዎችን ይለዋወጣሉ፤ ብሎም ከዘመድ አዝማድ ጋር በዓልን ያከብራሉ። በይበልጥ ግን፥ የአሏህን ፀጋዎች በማውሳት ስሙን እያላቁ የኢድ ሰላትን በመስጂዶች ይሰግዳሉ። ከእነዚህ ሁለት ቀናት ውጪ ሙስሊሞች በዓመቱ ውስጥ ለሌሎች ሐይማኖታዊ በዓላት እውቅና አይሰጡም፤ አያከብሩምም።

እርግጥ ነው እስልምና በተገቢው መንገድ እንዲከበሩ የሚፈቅዳቸው እንደ ሰርግ ወይም ሃቂቃ (ልጅ ሲወለድ የሚፈፀም) ያሉ ሌሎች የፌሽታ ጊዜያት አሉ። ይሁን እንጂ እንዲህ ያሉት ቀናት በዓመቱ ውስጥ ተለይተው የተቀመጡ ዕለታት አይደሉም፤ ይልቁንስ የሚከበሩት በአንድ ሙስሊሙ የሕይወት ኡደት ውስጥ አጋጣሚዎቹ በሚከሰቱባቸው ጊዜያት ነው።

በዒድ አል ፊጥርም ሆነ በዒድ አል አድሃ በዓላት፥ ጧት ላይ ሙስሊሞች በየመስጂዱ ተሰባስበው የዒድ ሶላት በህብረት እንደሰገዱ በማስከተልም ስላሉባቸው ሃላፊነቶችና ግዴታዎች የሚዘክር ምክረ ንግግር (ኹጥባህ) ከኢማሙ አንደበት ያደምጣሉ። ከሶላቱ በኋላ ሙስሊሞች "ኢድ ሙባረክ" (የተቀደሰ ኢድ) እየተባባሉ ስጦታዎችንና ጣፋጮችን ይለዋወጣሉ።

ኢድ አል-ፊጥር

ኢድ አል-ፊጥር የጨረቃ አቆጣጠርን በሚከተለው የእስልምና ካሌንደር ዘጠነኛ ወር ላይ የሚከናወነውን የረመዷን ፆም ፍቺ ያበስራል።

ኢድ አል-ፊጥር፥ ከሁሉም እጅግ የተቀደሱ ወራት ውስጥ አንዱን፥ ማለትም ረመዷንን፥ ተከትሎ የሚመጣ በመሆኑ በጣም አስፈላጊ ነው። ረመዷን፥ ሙስሊሞች ከአሏህ ጋር ያላቸውን ቁርኝት የሚያጠናክሩበት፣ ቁርዓን የሚቀሩበት እና በመልካም ሥራዎች ከፍ የሚሉበት ጊዜ ነው። በረመዷን ፍፃሜ ላይ፥ ሙስሊሞች ፆሙን በስኬት ስላጠናቀቁ እና የረመዷን ወርን በአምልኮ ተግባራት ተግተው በማሳለፋቸው፥ አሏህ የኢድ አል-ፊጥር ቀንን በሽልማት መልክ ይሰጣቸዋል። በኢድ አል-ፊጥር ዕለት፥ ሙስሊሞች ሌላ ረመዷንን ለመታደም፣ ወደርሱ ለመቅረብ፣ የተሻሉ ሰዎች ለመሆን እና ከጀሃነም እሳት ለመዳን ሌላ እድል ለማግኘት በመታደላቸው አሏህን ያመሰግናሉ።

ጦልሃ ቢን ዑበይዱሏህ (መልካም ስራቸውን አሏህ ይውደድላቸው) ባስተላለፉት ሐዲስ፥ ሁለት ሰዎች ወደ አላህ መልእክተኛ (ሰላም በእርሳቸው ላይ ይሁን) መጡ። ሁለቱም አብረው ነበር የሰለሙት። ነገር ግን አንደኛው ከሌላኛው ይበልጥ በአሏህ መንገድ ላይ ይጋደል ነበር። ይህ ታጋይ ሰው ለጂሐድ በወጣበት ተሰዋ። ሌላኛው ደግሞ ለአመት ያህል ቆይቶ ህይወቱ አለፈ። ጦልሃም እንዲህ አሉ፥ "በህልሜ በጀነት መግቢያ በር ላይ ሆኜ (እነዚያን ሁለት ሰዎች) አየኋቸው። የሆነ ሰው ከውስጥ ወጣና መጨረሻ ላይ የሞተውን ሰው ወደ ጀነት አስገባው። ከዚያም ተመልሶ ወጥቶ የተሰዋውን ሰው አስገባው። ከዚያም ወደ እኔ ተመልሶ መጣና 'ጊዜህ ገና ስላልደረሰ ተመለስ' አለኝ።" በማግሥቱ ጧት ጦልሃ ያዩትን ህልም ለሰዎች ባወሩ ጊዜ ግርምት ተፈጥሮ ነበር። ወሬው የአላህ መልእክተኛ (ሰላም በእርሳቸው ላይ ይሁን) ጋር በደረሰ ጊዜ ታሪኩን አጫወቷቸው። እርሳቸውም "ለምንድነው በዚህ የተገረማችሁት?" ብለው ጠየቋቸው። እነርሱም፥ "የአሏህ መልዕክተኛ ሆይ! በአሏህ መንገድ ላይ ይበልጥ የታገለውና በኋላም የተሰዋው የመጀመሪያው ሰውዬ ሆኖ ሳለ ወደ ጀነት ቀድሞት የገባው ግን ሌላኛው ነው።" የአላህ መልእክተኛም (ሰላም በእርሳቸው ላይ ይሁን) "ለዓመት ያህል በህይዎት ቆይቶ የለም ወይ?" ሲሉ ጠየቁ። "አዎ" አሉ። "ረመዷን መጥቶ ጾሞ የለ እንዴ? በዚያች ዓመትም እንዲህ እንዲያ ያሉ ሰላቶችን ሰግዶ የለ እንዴ?" አሏቸው። "አዎ" አሉ። የአሏህ መልእክተኛም (ሰላም በእርሳቸው ላይ ይሁን) እንዲህ አሉ፥ "በመካከላቸው ያለው ልዩነት በሰማይና በምድር መካከል ካለው ልዩነት ይበልጣል።"

Sunan Ibn Majah, 3925

ኢድ አል-አድሃ

ዒድ አል-አድሃ፥ የጨረቃን ኡደት መሰረት በሚያደርገው እስላማዊ የቀን መቁጠሪያ (ካሌንደር) በአስራ ሁለተኛውና የመጨረሻው ወር ዙል-ሂጃህ ውስጥ የሚከናዎነው፥ ዓመታዊ የሐጅ ስነስርዓት (ወደ መካ የሚደረግ መንፈሳዊ ጉዞ) ወቅት መጠናቀቁን ያበስራል።

ኢድ አል-አድሃ፥ ነብዩ ኢብራሂም (አብራሃም) ለአሏህ ፍፁም ታዛዥ ሆኖ ልጁን ኢስማዔልን (ኢሽማዒል) በመስዋዕትነት ለማቅረብ ያሳየውን ዝግጁነት ለመዘከር የሚከበር በዓል ነው። በዚያች የመሠዊያ ቁርጥ ሰዓት፥ በልጁ ምትክ ይታረድ ዘንድ አሏህ ኢስማኤልን በሙክት በግ ተክቶታል። ይህ ከአሏህ የመጣ ትእዛዝ፥ ነብዩ ኢብራሂም የጌታውን ትዕዛዝ ያለ አንዳች ጥያቄ ለመፈፀም ያለውን ፈቃደኝነትና ቁርጠኝነት የሚፈትን ነበር። በዚህም የተነሳ፥ ኢድ አል-አድሃ ማለት የመስዋዕት ክብረ በዓል ማለት ነው።

ሙስሊሞች በዒድ አል-አድሃ ላይ ከሚፈጽሟቸው ምርጥ ተግባራት አንዱ ከኢዱ ሶላት ቀጥሎ የሚደረገው የዑዱህያ (መስዋእትነት) እርድ ነው። ሙስሊሞች ነቢዩ ኢብራሂም ለአሏህ ብለው ያቀረቡትን መስዋዕት ለማስታወስ እንስሶች ያርዳሉ። ለእርድ የሚቀርበው እንስሳ ሙክት በግ፣ ጠቦት በግ፣ ፍየል፣ ላም፣ በሬ ወይም ግመል መሆን አለበት። እንስሳው በእስላማዊ ስርዓት ተቀባይነት ባለው (ሃላል) መንገድ ይታረድ ዘንድ በተሟላ አቋምና ጤንነት ከተወሰነ ዕድሜ ጣሪያ በላይ የሚገኝ መሆን አለበት። የታረደው እንስሳ ሥጋም ዑዱህያውን በፈፀመው ሰው፣ በወዳጅ ዘመዶቹ፣ እንዲሁም በድሆችና ችግርተኞች መካከል የሚከፋፈል ይሆናል።

በዒድ አል አድሃ ዕለት እንስሳ ማረድ ነብዩሏህ ኢብራሂም የገዛ ልጃቸውን በመሰዋዕትነት ለማቅረብ ያሳዩትን ፈቃደኛነት የሚዘክር ተግባር ነው። ይህም በቁርዓን ውስጥ የተወሳ የአምልኮ ተግባር እና የተረጋገጠ የነቢዩ ሙሐመድ (ሰላም በእርሳቸው ላይ ይሁን) ልማድም ነው።

ነብዩ (ሰላም በእርሳቸው ላይ ይሁን) ሁለት፥ ጥቁርና ነጭ ቀለም ያላቸው፥ የበግ ሙክቶችን (በመስዋዕትነት) አጋድመው እግራቸውን ሽንጣቸው ላይ በመጫን የአላህን ስም ሲጠሩና ተክቢራ (አሏሁ አክበር) ሲሉ አየሁ። ከዚያም በራሳቸው እጅ አረዷቸው።

Sahih al-Bukhari, 5558

አሏህ በቁርዓን እንዲህ ብሏል፦

ሐጅንና ዑምራንም ለአላህ ሙሉ። ብትታገዱም ከሀድይ (ከመሥዋእት) የተገራውን (መሰዋት) አለባችሁ። (. . .)

ቁራኣን - 2:196
(ፍቹ ሲተረጎም)

ምንጭ: islamqa.info
ትርጉም በ: Abdu Ahmed

ተመሳሳይ ጥያቄዎች