ነቢዩ ሙሐመድ ማን ናቸው?

ሙሐመድ (ሰላም በእርሳቸው ላይ ይሁን) በ570 (እ.ኤ.አ) በመካ ተወለዱ። አባታቸው እርሳቸው ከመወለዳቸው በፊት በመሞታቸውና እናታቸውም ብዙ ሳይቆዩ በልጅነታቸው ስለተከተሉ ያሳደጓቸው ከተከበረው የቁረይሽ ጎሳ የሆኑት አጎታቸው ነበሩ። ያደጉት መሃይም ሆነው፥ ማንበብና መጻፍ ሳይማሩ፥ ሲሆን እስከ ህልፈታቸው ድረስ እንዲያ ሆነው ነበር የኖሩት። ከነብይነት ተልዕኳቸው በፊት፥ ህዝባቸው ከሳይንስ የራቀና ባብዛኛውም መሃይም ነበር። በእድሜ እየጎለመሱ ሲመጡ፥ እውነተኛ፣ ቅን፣ ታማኝ፣ ለጋስ እና ትሁት መሆናቸው ተመስክሮላቸው ነበር። እጅግ ሲበዛ ታማኝ ስለነበሩም ህዝቡ ታማኙ እያለ ይጠራቸውም ነበር። ሙሐመድ (ሰላም በእርሳቸው ላይ ይሁን) በእጅጉ መንፈሳዊ ስለነበሩ፥ የማህበረሰባቸውን የሞራል ዝቅጠትና ጣዖት አምላኪነት ከድሮውም ይጸየፉ ነበር።

በአርባኛ አመታቸው፥ ሙሐመድ (ሰላም በእርሳቸው ላይ ይሁን) በመልአኩ ገብርኤል (ጂብሪል) አማካኝነት የመጀመሪያው መልዕክት ከአሏህ ወረደላቸው። መልዕክቶቹ ለቀጣዮቹ ሃያ ሶስት አመታት መውረዳቸውን ቀጥለው የነበረ ሲሆን፥ ጠቅላላ ስብስባቸውም ቁርዓን በመባል ይታወቃል።

ቁርዓኑን መቅራትና አሏህ የገለጠላቸውን እውነታ መስበክ እንደጀመሩ፥ በአሏህ የካዱ ኢአማኞች እሳቸውንና በጣት የሚቆጠሩትን ተከታዮቻችውን ማሳደድና ማሰቃየት አመጡ። ማሳደዱና ማሰቃየቱ እጅግ እየበረታ ሄዶ በ622 (እ.አ.አ) አሏህ ይሰደዱ ዘንድ ትእዛዝ አወረደላቸው። ይህ ከመካ በስተሰሜን 418 ኪሎ ሜትር አካባቢ ርቃ ወደምትገኘው መዲና ከተማ የተደረገው የስደት ጉዞ የሙስሊሞችን የቀን መቁጠሪያ ካላንደር መጀመር ያበስራል።

ከበርካታ አመታት በኋላ ነብዩ ሙሐመድ (ሰላም በእርሳቸው ላይ ይሁን) እና ተከታዮቻቸው ወደ መካ በድል አድራጊነት መመለስ ችለው የነበረ ሲሆን፥ ለጠላቶቻቸውም ምህረትን አድርገዋል። ነብዩ ሙሐመድ (ሰላም በእርሳቸው ላይ ይሁን) በስልሳ ሶስት አመት እድሜያቸው ይህችን አለም ከመሰናበታቸው በፊት የአረብ ባሕረ ሰላጤ ሰፊው ክፍል ሰልሞ ነበር፤ ብሎም እርሳቸው ባለፉ በአንድ ምዕተ አመት ውስጥ እስልምና በምዕራቡ ዓለም ስፔንን ተሻግሮ በምስራቁ አለም ደግሞ ቻይና ድረስ ተስፋፍቶ ነበር። ለእስልምና ሐይማኖት በፍጥነት እና በሰላማዊ መንገድ መስፋፋት ምክንያት ከሆኑ ጉዳዮች መካከል የአስተምህሮቱ እውነተኛነትና ግልጽነት ተጠቃሽ ነው። የእስልምና ጥሪ በዚያ ሊመለክ በሚገባው አንዱ አምላክ ብቻ ማመን ነው።

ነቢዩ ሙሐመድ (ሰላም በእርሳቸው ላይ ይሁን) ቅን፣ ፍትሃዊ፣ ሩህሩህ፣ አዛኝ፣ እውነተኛ እና ጀግና የሰው ልጅ ፍጹም ምሳሌ ነበሩ። ሰው ቢሆኑም፥ ከመጥፎ ባህሪያት ሁሉ የተጥራሩ ነበሩ፤ ለአሏህ ውዴታና በወዲያኛው ዓለም ሽልማቱን ለመጓናፅፍ ብለው ብቻም ይታትሩ ነበር። ከዚህም ባሻገር፥ በሚያደርጓቸው ነገሮችና በጉዳዮቻቸው ሁሉ ምንጊዜም ስለአሏህ የሚጨነቁና አሏህንም ፈሪ ነበሩ።

ምንጭ: islam-guide.com
ትርጉም በ: Abdu Ahmed

ተመሳሳይ ጥያቄዎች