ቁርዓንን የፃፈው ማን ነው?

አሏህ የመጨረሻውን ነብይ ሙሐመድን (ሰላም በእርሳቸው ላይ ይሁን) ከእርሱ የተላኩ እውነተኛ ነብይ መሆናቸውን ባረጋገጡ በርካታ ተዓምራትና ብዙ ማስረጃዎች ደግፏቸዋል። በተጨማሪም፥ አሏህ የመጨረሻ መፅሃፉን፥ ቅዱስ ቁርዓንን፥ የራሱ ቀጥተኛ ቃል፣ ራሱ ያወረደው እና የማንም ሰው እጅ ያልገባበት መሆኑን በሚያረጋግጡ በርካታ ተዓምራት ደግፎታል።

ቁርዓን፥ አሏህ ለነብዩ ሙሐመድ (ሰላም በእርሳቸው ላይ ይሁን) በመልዕክተኛው ጂብሪል በኩል ያወረደላቸው የራሱ ቀጥተኛ ቃል ነው። ነብዩ ሙሐመድ (ሰላም በእርሳቸው ላይ ይሁን) በልባቸው ሃፍዘው ከዚያም ለባልደረቦቻቸው በቃል አስጠንተዋቸዋል። እነርሱም በተራቸው በልቦቻቸው በመሃፈዝ፥ በፅሁፍም በማስፈር ከነብዩ ሙሐመድ (ሰላም በእርሳቸው ላይ ይሁን) ጋር ሆነው ገምግመውታል። ከዚህም ባሻገር፥ ነብዩ ሙሐመድ (ሰላም በእርሳቸው ላይ ይሁን) በያመቱ ለአንድ ለአንድ ጊዜ፥ በህይወታቸው የመጨረሻው አመት ደግሞ ለሁለት ጊዜያት ቁርዓንን ከመልአኩ ጂብሪል ጋር ገምግመዋል። ቁርዓን ከወረደበት ጊዜ አንስቶ እስካሁኗ እለት ድረስ፥ ቁርዓንን ፊደል በፊደል በልቦናዎቻቸው የሃፈዙ እጅግ በርካታ ቁጥር ያላቸው ሙስሊሞች ሁሌም ነበሩ። አንዳንዶቹ እንዲያውም በአስር አመት እድሜያቸው ሙሉውን ቁርዓን ለመሃፈዝ ችለዋል። ባለፉት ምዕተ አመታት አንዲትም የቁርዓን ፊደል አልተለወጠችም።

ከአስራ አራት ምዕተ አመታት በፊት የወረደው ቁርዓን፥ በቅርብ ጊዜያት በሳይንቲስቶች የተደረሰባቸው ወይም የተረጋገጡ እውነታዎችን ጠቅሷል። ይህም ቁርዓን የአሏህ ቀጥተኛ ቃል መሆን እንዳለበት፥ በነብዩ ሙሐመድ (ሰላም በእርሳቸው ላይ ይሁን) ላይ ራሱ እንዳወረደላቸው እና ቁርዓን በነብዩ ሙሐመድም (ሰላም በእርሳቸው ላይ ይሁን) ሆነ በሌላ በየትኛውም የሰው ዘር እንዳልተፃፈ ያለጥርጥር ያረጋግጣል። ሌላ የሰው ልጅ ። ይህ በተጨማሪ ነብዩ ሙሐመድ (ሰላም በእርሳቸው ላይ ይሁን) በእውነትም ከአሏህ የተላኩ ነብይ መሆናቸውን ያረጋግጣል። ምጡቅ መሳሪያዎችን እና የተራቀቁ ሳይንሳዊ ዘዴዎችን በመጠቀም በቅርብ ጊዜ የተደረሰባቸውን ወይም የተረጋገጡትን እነዚህን እውነታዎች፥ ከአስራ አራት ምዕተ አመታት በፊት የሚያውቅ ሰው ሊኖር እንደሚችል ማሰብ ከአእምሮ በላይ ነው።

ምንጭ: islam-guide.com
ትርጉም በ: Abdu Ahmed

ተመሳሳይ ጥያቄዎች