ሙስሊም ሴቶች ለምን ሒጃብ ይለብሳሉ?

ሒጃብ የሚለው ቃል የተመሰረተው 'ሀጀበ' ከሚለው የአረብኛ ስርወ ቃል ሲሆን መደበቅ ወይም መሸፈን የሚል ፍች አለው። በኢስላማዊ አውድ ውስጥ፥ ሒጃብ ለአቅመ ሔዋን የደረሱ ሙስሊም ሴቶች የሚጠበቅባቸውን የአለባበስ ሥርዓት ያመለክታል። ሒጃብ ከፊትና ከእጅ በስተቀር መላ አካልን የመሸፈን ወይም የመከናነብ ግዴታን የሚመለከት ነው። አንዳንዶች ፊታቸውን እና እጆቻቸውን ጭምር መሸፈንን ይመርጣሉ። ይህም ቡርቃ ወይም ኒቃብ ተብሎ ይጠራል።

ሒጃብን ለማስጠበቅ ሙስሊም ሴቶች የቅርብ ዝምድና በሌላቸው ወንዶች ፊት የሰውነት ቅርጻቸውን በማያጋልጡ አልባሳት ገላቸውን በአግባቡ መሰተር ይጠበቅባቸዋል። ይሁን እንጂ፥ የሒጃብ ጉዳይ ውጫዊ ገጽታዎችን ስለመሰተር ብቻ አይደለም፤ ስለ መልካም ንግግር፣ ጨዋ ምግባር እና ክብር ስለተሞላበት ጠባይም ጭምር ነው።

አንተ ነቢዩ ሆይ! ለሚስቶቸህ፣ ለሴቶች ልጆችህም፣ ለምእምናን ሚስቶችም ከመከናነቢያዎቻቸው በላያቸው ላይ እንዲለቁ ንገራቸው፡፡ ይህ እንዲታወቁና (በባለጌዎች) እንዳይደፈሩ ለመኾን በጣም የቀረበ ነው፡፡ አላህም መሓሪ አዛኝ ነው፡፡

ቁራኣን - 33:59
(ፍቹ ሲተረጎም)

ሒጃብ ብዙ ጥቅሞች ያሉት ቢሆንም ሙስሊም ሴቶች ሒጃብን የሚያጠብቁበት ቁልፍ ምክንያት የአሏህ ትእዛዝ በመሆኑ ነው። እሱ ደግሞ ለፈጠራቸው ፍጡራን እጅግ የሚበጃቸው ምን እንደሆነ ያውቃል።

ከውጫዊ ገጽታዋ ይልቅ ውስጣዊ የመንፈስ ውበቷን በማጉላት ሒጃብ ሴትን ልጅ ያጎለብታል። ክብራቸው እንደተጠበቀ ሆኖ በንቃት የሚሳተፉ የማህበረሰብ አባላት እንዲሆኑ ሴቶችን ነፃነት ያጎናፅፋል።

ሒጃብ መጨቆንን፣ መረገጥን ወይም መታፈንን አያመለክትም። ይልቁንስ ክብረ ነክ ዘለፋዎችን፣ ያልተፈለጉ ጉንተላዎችን እና ኢፍትሃዊ አድልዖዎችን መከላከያ ልባስ ነው። ስለዚህ በቀጣይ አንዲት ሒጃብ ያደረገች ሙስሊም ሴት ባያችሁ ጊዜ የተከናነበችው አካላዊ ቁመናዋን እንጂ አእምሮዋን ወይም አስተሳሰቧን እንዳልሆነ እወቁ።

ምንጭ: islamicpamphlets.com · islamicpamphlets.com
ትርጉም በ: Abdu Ahmed